በአንድ እርምጃ

የዘላለም ሕይወት

ዘላለማዊ ፍጻሜዎን የሚያረጋግጥ ውሳኔ

ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግንኙነት መመስረት፤

እውነተኛ እርካታንና መልካም ፍጻሜን ማግኘት::

ምርጫህ የዘላለም ሕይወት ይሁን

የሕይወትህን አቅጣጫና የዘላለም እጣ ፈንታህን መወሰን የምትችለው በምድር ላይ አንተ ብቻ እንደሆንክ ታውቃለህ? በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠርክ ክቡር ፍጥረት ነህ። እግዚአብሔር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይወድሀል። እንደሸክም የተጫነህን ነገር ሁሉ አስወግዶ የመንግስቱ ወራሽ ሊያደርግህ ሁልጊዜ ዝግጁ ሆኖና እጆቹን ዘርግቶ እየጠበቀህ ነው። ይሁን እንጂ ወሳኙ አንተ በነጻ ፈቃድህ የምትወስነው ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ለአንተ የሞት የሽረት ውሳኔ ስለሆነ ችላ ብለህ ልታልፈው አይገባም፡፡

እያንዳንዱ ቀን ንስሃ እንድትገባና ወደ እግዚአብሔር እንድትመለስ የተሰጠህ ወርቃማ እድል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ያለውን የሕይወት አጭርነት ለመግለጽ ቶሎ ታይቶ ወዲያው የሚጠፋውን እንፋሎት እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። በእርግጥም በዚህ ዓለም ያለን እድሜ ውስን ነው። በሌላ በኩል፣ በዚህ ምድር ላይ ካለን ጊዜያዊ ሕልውና በላይ የሆነ የዘላለም ሕይወት አለ።  እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው እንዲድንና የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ይፈልጋል። ይህን የእግዚአብሔርን ምህረት ተጠቅመህ የዘላለም እጣ ፈንታህን መወሰን የምትችለው በአካል ህያው ሆነህ እያለህ ብቻ ነው።

አካላዊ ሞት የማይቀር ክስተት ነው፤ በእርግጥ ሁሉም ሰው አንድ ቀን ይሞታል፤ ነገር ግን ሁለተኛ ሞት እንዳለ ታውቃለህ? በመጀመሪያ የሰው ልጅ የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖረው ነበር፣ ነገር ግን በአዳምና በሔዋን ኃጢአት ምክንያት ሰው ከእግዚአብሔር ተለየ። በዚህም ምክንያት መላው የሰው ልጅ ኃጢአተኛ ሆነ፤ በመንፈስም ሙት ሆነ። የእግዚአብሔር ቃል “ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል”ይላል፡፡ (ሮሜ 3፡23) ቀጥሎም በዚሁ በሮሜ መጽሐፍ 6፡23 ላይ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” ይላል።

ወዳጄ ሆይ፣ አንተም የአዳም ዘር ስለሆንክ ኃጢአተኛ ነህ። ኃጢአት ከእግዚአብሔር ይለያል እናም በመጨረሻ የገሃነምን ቅጣት ያስከትላል። ገሃነም የእሳት ባሕር ነው እርሱም ሁለተኛው ሞት ነው። “በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባህር ውስጥ ተጣለ፡፡” (ራዕይ 20፡15) እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ወደ ራሱ የሚሰበስብበት እና ለእያንዳንዱን እንደ ሥራው የሚከፍልበት ጊዜ ይመጣል። ማቴዎስ 13፡49-50 እንዲህ ይለናል “በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል መላዕክት መጥተው ኃጢያተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩዋቸዋል፤ ወደ አቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፡፡ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡” ይህ የሰው ቃል ሳይሆን ሰማይንና ምድርን የፈጠረው የሕያው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህን ቃል ከፍተኛ ትኩረት ልትሰጠውና ልታምነው ይገባሃል፡፡. ባታምነውም  እንኳ መፈጸሙ የማይቀር መሆኑን አስታውስ።

ገሃነም የዘላለም ስቃይ ቦታ ነው። ወደዚህ ዘግናኝ ቦታ የምትጣለውም ሆነ ከዚያ መዳን የምትችለው ዛሬ በምድር ላይ እያለህ  በምትመርጠው ምርጫና በምትወስነው የግል ውሳኔ ብቻ ነው። ታዲያ ከዚህ ዘላለማዊ ስቃይ ማምለጥ ስትችል ለምን ወደዚያ ትሄዳለህ? ከዚህ ከዘላለማዊ እሳት እና ስቃይ መዳን ከፈለክ ኃጢአትህን ለኢየሱስ ክርስቶስ ተናዘዝና ይቅር እንዲልህ ለምነው። እርሱም ኃጢአትህን ይቅር ይልሃል፤ ወደ መንግሥተ ሰማያትም በነፃነት ያስገባሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “በኃጢያታችን ብንናዝ ኃጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአመፃም ሁሉ ሊያነፃን  የታመነና ጻድቅ ነው፡፡”ይላል (1ኛ ዮሐንስ 1፡9) ነገር ግን ንስሐ ሳትገባ በኃጢአትህ መቀጠልን  ከመረጥህ  ለዘላለሙ በገሃነም እንደምትጣል እርግጠኛ ሁን።

በንብረትህ፣ በራስህ ጽድቅ ወይም ወይም በሌላ በማናቸውም ነገር የምትታመን ከሆነ ይህ አባባል ሞኝነት ሊመስልህ ይችላል፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ሀብት፣ ስልጣን፣ ዝና፣ ክብር፣ የቅርብ ወዳጆች፣ ዘመድ አዝማድ፣ ትምህርት፣ እውቀት፣ ልምድ፣ ውበት፣ ጥንካሬ፣ በራስ መተማመን ወይም ሌላ ምንም ዓይነት ነገር ቢኖርህ አንድ ቀን መሞትህ የማይቀር መሆኑንና ከዚያም በእግዚአብሔር የፍርድ  ዙፋን ፊት እንደምትቆም እወቅ። “ጌታ ኢየሱስም በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላዕክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አህዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፡፡ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፡፡ በጎቹን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል፡፡ ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፡፡” (ማቴዎስ 25፡31-34)“በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመላዕክቱ ወደተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ፡፡” (ማቴዎስ 25፡41)

በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ከ150,000 በላይ ሰዎች ይሞታሉ። የተፈጥሮ ህግ ነውና እንደነዚህ ግለሰቦች አንድ ቀን አንተም ከዚህ አለም  በሞት ትለያለህ፡፡ ኃጢአትህን ለኢየሱስ ክርስቶስ ተናዘህ እርሱን እንደ ግል አዳኝህ ካልተቀበልከው ከዚያም ቀጥሎ ሁለተኛውን ሞት ሞተህ ወደ ገሃነም ትገባለህ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአትና ከሚያሰከትለው መዘዝ ሁሉ ሊያድንህ ከሰማየ ሰማያት መጣ፣ ስለ አንተ ተሰቃየ፣  ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ የኃጢአትንም ቅጣት በሞት ከፈለ። በአንተ ቦታ አርሱ ኃጢአተኛ ሆነ። ኃጢአትህ ይደመሰስ ዘንድ በቀራንዮ ተራራ በመስቀል ላይ  ደሙን አፈሰሰ፣ ነፍሱንም ስለ አንተ አሳልፎ ሰጠ፤. በትንሣኤው የዘላለም ሕይወትን እንድታገኝ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል ነሥቶ ከሙታን ተነሣ። ዳግመኛም ይመጣል፤ በእርሱ የሚያምኑትንም ይወስዳቸዋል። “ሁለተኛም እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ፡፡” (ዮሐንስ 14፡3)  በእርሱ ካላመንህ ግን የሚመጣው ሊፈርድብህ ነው። “ከእኔ ተለይተህ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ሂድ” ይልሃል፡፡“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡” (ዮሐንስ 3፡16)  አየሱስ ክርሰቶስ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ ለአንተ በነጻ የሰጠህን ይህን ታላቅ መዳን ቸል ብትል አይፈርድብህምን? በእርግጥ ይፈርድብሃል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው አንተን ከኃጢአትህ ሊያነጻህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢያት ሁሉ ያነጻናል” ይላል (1ኛ ዮሐንስ 1፡7) ከገሃነም ስቃይ ነፃ የሚያወጣህና የዘላለም ህይወት የሚሰጥህ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሎ በዮሐንስ ወንጌል 14፡16 በግልጽ በቃሉ ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋሪያት ሥራ 4፡12 ላይ “መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” በማለት በግልጽ ይናገራል። “እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው፡፡” (2ኛ ቆሮ. 6፡2) ነገ ምን እንደሚሆን አታውቅም፤ ነገ ያንተ አይደለምና አሁኑኑ ኃጢያትህን ለኢየሱስ ክርስቶስ ተናዘዝና እመነው፤ ወደ ሕይወትህም ጋብዘው፡፡ 

ከዘላለም ፍርድ ለመዳንና የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ትፈልጋለህን?

  1. ኃጢአተኛ እንደሆንክ እና ከኃጢአትህ በራስህ ኃይል መንጻት እንደማትችል እመን።
  2. ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንተ ኃጢያት እንደሞተና በትንሳኤውም የዘላለምን ሕይወት እንድታገኝ ከሞት እንደተነሣ እመን።
  3. ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታህ እና እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ ተቀበል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያትህን እዳ ለመክፈል በመስቀል ላይ መሞቱንና ለአንተ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መነሳቱን አምነህ አሁን እንደ ጌታህና አዳኝህ ልትቀበለው ትፈልጋለህ? መልስህ አዎን ከሆነ ይህን ጸሎት ጸልይ ፡- “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፣ ለኃጢአቴ በመስቀል ላይ እንደሞትክ፣ እንደተቀበርክ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደተነሳህ ዳግመኛም እንደምትመጣ አምናለሁ፣ ጌታ አየሱስ ሆይ ኃጢያቴን ይቅር በለኝ፣ በከበረው ደምህ እጠበኝ፣ ወደ ልቤም ግባ፣ እንደ ጌታዬና የግል አዳኜ አድርጌ አሁን በእምነት እቀበልሃለሁ፣ ይቅር ስላልከኝ አመሰግንሃለሁ፤ አሜን።

ይህን ጸሎት በቅንነት ከጸለይክ፣ አሁን ከዘላለም ፍርድ እና ከገሃነም ድነሃል፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ሆነሃል ። ያለጥርጥር የመንግሥተ ሰማያት ወራሽ ሆነሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” ይላል። (ዮሐንስ 1 ፡12) ይህ በህይወትህ ፈጽሞ የማትጸጸትበት ታላቅ ውሳኔ ነው!

ይህን ጸሎት ከጸለይክ እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቅህ ቀጥሎ ማድረግ የሚገባህ ተግባሮች የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አንብብ። በመጀመሪያ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን የወንጌል መጻሕፍት አንብብ።
  2. በየቀኑ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገር።
  3. በመጽሐፍ ቅዱስ በምታምን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በመሄድ እግዚአብሔርን ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር አምልክ።
  4. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትከተል ለሌሎች መስከር። “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና” (ሮሜ 10፡9)

የሚቀድስህ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራህ፣ የሚያስተምርህና ሀይልን የሚሰጥህ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱሰን ትሞላ ዘንድ የጌታ የኢየሱስን ስም ጠርተህ ጋብዘው፡፡ ይህን በማድረግ በመንፈስ ቅዱስ ትሞላለህ ።  በሉቃስ 11፡13 ላይ “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው” ይላል፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ከመልካምና እና ከክፉ፣ ከበረከትና ከመርገም፣ ወደ ዘላለማዊ ህይወት ከሚወስደውና  እና ወደ ገሃነም ከሚወስደው መንገድ መካከል እንድትመርጥ ነጻ ፈቃድ ሰጥቶሃል። ኃጢአትህን ከተናዘዝክና ኢየሱስን እንደ ጌታህና አዳኝህ ከተቀበልክ የዘላለምን ሕይወት መርጠሃል። ነገር ግን ይህንን ጥሪ ችላ ብለህ በኃጢያትህ ከጸናህ፣ የዘላለም ሞትን መርጠህ ወደ ገሃነም እያመራህ ነው። ” በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።” (ዮሐንስ 3፡18)

ውሳኔህ ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ልጅ መሆንና በእግዚአብሔር መንግሥት የዘላለምን ሕይወት መኖር ወይስ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ በተዘጋጀው የእሳት ባሕር ውስጥ ለዘለዓለም መጣል?

ማንኛውም ጥያቄ ካሎት በዚህ አድራሻ mygreatdecision@gmail.com ኢሜይል ይላኩልን።

እንኳን ደህና መጡ

እንኳን ወደ ድረ ገጻችን በደህና መጡ! ይህ ድረ ገጽ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለተሰጠው የዘላለም ሕይወት ሰዎችን ሁሉ ለማሳወቅ እና አምነውም  የዘላለም ሕይወት  ለመቀበል እንዲወስኑ ለመርዳት ታሰቦ የተዘጋጀ ነው።  ዓለማው ወንጌልን መስበክ እና መንፈሳዊ እድገትን መደገፍ ነው። ያለምንም ማመቻች እውነቱን ሳይጨመር ሳይቀነስ እናቀርባለን፡፡ መልእክቱ ለሁሉም ህዝብ፣ ለሁሉም ሰው፣ እና ለሁሉም ልብ ነው። ለሕይወት ጥልቅ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት፣ ውስጣዊ ሰላምን ለመጎናጸፍ፣ ከመጨረሻው ፍርድ ለመዳንና የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ የሚፈልጉ ከሆነ ወደ ትክክለኛ ቦታ መጥተዋል። የዘላለምን ህይወት ይቀበሉ እና ከገሃነም ያምልጡ። በእግዚአብሔር ላይ ያለዎትን እምነት ያሳድጉ፣በእውነተኛ እርካታ የተሞላ ሕይወት መኖር ይጀምሩ። በዚህ ቅዱስ መንገድ አብረን እንጓዝ።

ያነጋግሩን

ከእርስዎ  ለመስማት እንወዳለን።  ጥያቄ አልዎት?  ወይስ ስለ አገልግሎታችን ይበልጥ ለማወቅ ይፈልጋሉ? ያነጋገሩን። እኛን ለማግኘት እባክዎ ኢሜይል ይላኩልን ወይም በአድራሻ ገጽ ላይ ያለውን ቅጽ ይሙሉ፡፡ የእርስዎን ሀሳብ ለመስማትና ጥያቄዎን ለመመለስ ሁልጊዜም ዝግጁ ነን፡፡